ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5
  6. 6

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጢሞቴዎስ 6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ስምና ትምህርቱም እንዳ ይሰደቡ፣ በባርነት ቀንበር ሥር ያሉ ሁሉ፣ ጌቶቻቸው ሙሉ ክብር እንደሚገባቸው አድርገው ይቊጠሩ።

2. የሚያምኑ ጌቶች ያሏቸውም፣ ወንድሞች ስለሆኑ የሚገባቸውን ክብር አይንፈጓቸው፤ ይልቁንም በአገልግሎታቸው የሚጠቀሙ አማኞችና ወዳጆቻቸው ስለሆኑ የበለጠ ሊያገለግሏቸው ይገባል። እነዚህን ነገሮች አስተምር፤ ምከርም።

የገንዘብ ፍቅር

3. ማንም የሐሰት ትምህርት ቢያስተምር፣ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጤናማ ቃልና እውነተኛ መንፈሳዊነትን ከሚያጐለብት ትምህርት ጋር የማይስማማ ቢሆን፣

4. ያ ሰው በትዕቢት ተወጥሮአል፤ አንዳችም አያስተውልም። ስለ ቃላት ለመከራከርና ለመጣላት ክፉ ጒጒት አለው፤ እነዚህም ቅናትን፣ ጥልን፣ ስድብን፣ መጥፎ ጥርጣሬን ያስከትላሉ፤

5. እውነትን በተቀሙና መንፈሳዊው ነገር ትርፍ ማግኛ በሚመስላቸውና አእምሮ በጐደላቸው ሰዎች መካከል የማያባራ ንትርክ ያመጣሉ።

6. ነገር ግን እውነተኛ መንፈሳዊነት ባለን ነገር ከመርካት ጋር ትልቅ ትርፍ ነው።

7. ምክንያቱም ወደ ዓለም ያመጣነው ምንም ነገር የለም፤ ምንም ነገር ይዘን መሄድም አንችልም።

8. ነገር ግን ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል።

9. ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ግን ወደ ፈተናና ወደ ወጥመድ፣ እንዲሁም ሰዎችን ወደ መፍረስና ወደ ጥፋት ወደሚያዘቅጠው ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት ይወድቃሉ።

10. ምክንያቱም የገንዘብ ፍቅር የክፋት ሁሉ ሥር ነው፤ አንዳንዶች ባለጠጋ ለመሆን ካላቸው ጒጒት የተነሣ ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል፤ ራሳቸውንም በብዙ ሥቃይ ወግተዋል።

ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ዐደራ

11. የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ አንተ ግን ከዚህ ሁሉ ሽሽ፤ ጽድቅን፣ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወትን፣ እምነትን፣ ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ገርነትን ተከታተል።

12. መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የመሰከርህለትንና የተጠራህበትን የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ያዝ።

13. ለሁሉም ሕይወትን በሚሰጥ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲሁም በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት እውነትን በመሰከረ በክርስቶስ ኢየሱስ ፊት ዐደራ የምልህ፣

14. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስኪገለጥ ድረስ፣ ይህን ትእዛዝ ያለ ዕድፍና ያለ ነቀፋ ሆነህ እንድትጠብቅ ነው፤

15. ያም መገለጥ፣ የተባረከውና ብቻውን ገዥ የሆነው የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶችም ጌታ እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ የሚያሳየው ነው፤

16. እርሱ ብቻ ኢመዋቲ ነው፤ ሊቀረብ በማይቻል ብርሃን ውስጥ ይኖራል፤ እርሱን ያየ ማንም የለም፤ ሊያየውም የሚችል የለም። ለእርሱ ክብርና ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን።

17. በዚህ ዓለም ባለጠጎች የሆኑት እንዳይታበዩ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ በሚሰጠን በእግዚአብሔር እንጂ አስተማማኝነት በሌለው በሀብት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።

18. መልካም እንዲሠሩ፣ ቸሮችና ለማካፈል ፈቃደኞች የሆኑ እንዲሆኑ እዘዛቸው።

19. በዚህ ዐይነት እውነተኛ የሆነውን ሕይወት ያገኙ ዘንድ፣ ለሚመጣው ዘመን ጽኑ መሠረት የሚሆን ሀብት ለራሳቸው ያከማቻሉ።

20. ጢሞቴዎስ ሆይ፤ በዐደራ የተቀበልኸውን ሁሉ ጠብቅ፤ እግዚአብሔርን ከማያስከብር ከከንቱ ልፍለፋና ለተቃውሞ በውሸት ዕውቀት ከተባለ ፍልስፍና ራቅ፤

21. የዚህ ዐይነት ዕውቀት አለን ሲሉ የነበሩ አንዳንዶች ይህን በማድረጋቸው ከእምነት መንገድ ስተው ሄደዋል።