ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጢሞቴዎስ 5:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. አረጋዊውን ሰው እንደ አባትህ ቈጥረህ ምከረው እንጂ በኀይለ ቃል አትናገረው። ወጣት ወንዶችን እንደ ወንድሞች ተቀበላቸው፤

2. እንዲሁም አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና አስተናግዳቸው።

3. በርግጥ ችግረኛ የሆኑትን መበለቶች ተን ከባከባቸው።

4. አንዲት መበለት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሯት፣ እነዚህ ልጆች የራሳቸውን ቤተ ሰብ በመርዳትና ለወላጆቻቸውም ብድራትን በመመለስ ከሁሉ በፊት እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መማር ይገባቸዋል፤ ይህ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነውና።

5. በርግጥ መበለት የሆነች፣ ብቻዋንም የምትኖር ተስፋዋን በእግዚአብሔር ላይ ታደርጋለች፤ ለጸሎትና የእግዚአብሔርን ርዳታ ለመለመን ሌሊትና ቀን ትተጋለች።

6. ምድራዊ ደስታን የምትሻዋ መበለት ግን በሕይወት ብትኖርም የሞተችናት።

7. ማንም የሚነቀፍበት ነገር እንዳይኖር፣ ይህንም ትእዛዝ ለሕዝቡ ስጥ።

8. አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ ሃይማኖቱን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።

9. ዕድሜዋ ከሥልሳ ዓመት ያነሰ መበለት በመዝገብ ላይ አትጻፍ፤ ደግሞም የአንድ ባል ሚስት የነበረች ልትሆን ይገባል፤

10. ልጆችን በማሳደግ፣ እንግዶችን በመቀበል፣ የቅዱሳንን እግር በማጠብ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለበጎ ምግባር ሁሉ ራሷን በመስጠት በመልካም ሥራም የተመሰከረላት መሆን አለባት።

11. ወጣት መበለቶችን ግን እንዲህ ባለው መዝገብ አትጻፋቸው፤ ምክንያቱም ሥጋዊ ፍላጎታቸው ለክርስቶስ በገቡት ቃል ላይ በሚያይልበት ጊዜ ለማግባት ይሻሉና።

12. በዚህም ፍርድን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፤ በመጀመሪያ የገቡትን ቃል ኪዳን አፍርሰዋልና።

13. በተጨማሪም ሥራ መፍታትንና ከቤት ቤት መዞርን ይለምዳሉ፤ ሥራ ፈት መሆን ብቻ ሳይሆን፣ የማይገባውን እየተናገሩ ሐሜተኞችና በሰው ጒዳይም ጣልቃ የሚገቡ ይሆናሉ።

14. ስለዚህ ባል የሞተባቸው ወጣት ሴቶች እንዲያገቡ፣ ልጆች እንዲወልዱ፣ ቤታቸውን እንዲያስተዳድሩ፣ ጠላትም የሚነቅፍባቸውን ነገር እንዳያገኝ እመክራለሁ።

15. በርግጥ ከዚህ በፊት አንዳንዶቹ ሰይጣንን ለመከተል ዘወር ብለዋል።

16. አማኝ የሆነች ማንኛዋም ሴት በቤተ ሰቧ ውስጥ መበለቶች ቢኖሯት፣ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ መበለቶችን ብቻ መርዳት እንድትችል እርሷው ትርዳቸው እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ሸክም እንዲሆኑ አትተዋቸው።

17. ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ የሚያስተዳድሩ፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች ዕጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤

18. መጽሐፍም፣ “እያበራየያለውን በሬ አፉን አትሠር፤” ደግሞም፣ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ይላልና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጢሞቴዎስ 5