ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ጢሞቴዎስ 1:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. የዚህ ትእዛዝ ዐላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው።

6. አንዳንዶች ከእነዚህ ነገሮች ዘወር ብለው ወደ ከንቱ ንግግር ተመልሰዋል።

7. የሕግ መምህራን ለመሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ስለሚናገሩት ወይም አስረግጠው ስለሚሟገቱለት ነገር አያውቁም።

8. ነገር ግን ሰው በአግባቡ ከተጠቀመበት፣ ሕግ መልካም መሆኑን እናውቃለን።

9. ደግሞም ሕግ የተሰጠው ለጻድቃን ሳይሆን፣ ለሕግ ተላላፊዎችና ለዐመፀኞች፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ለሌላቸውና ለኀጢአተኞች፣ ቅድስና ለሌላቸውና እግዚአብሔርን ለሚንቁ፣ አባትና እናታቸውን ለሚገድሉ፣ ለነፍሰ ገዳዮች መሆኑን እናውቃለን፤

10. እንዲሁም ለዘማውያን፣ ከወንድ ጋር ለሚተኙ ወንዶች፣ ሰውን ለሚሸጡና ለሚገዙ፣ ለውሸተኞች፣ በሐሰት ለሚምሉ፣ ጤናማ የሆነውን ትምህርት ለሚጻረሩ ሁሉ ነው፤

11. ይህ ጤናማ ትምህርት ቡሩክ እግዚአብሔር ለእኔ በዐደራ ከሰጠኝ የክብር ወንጌል ጋር የሚስማማ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ጢሞቴዎስ 1