ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 5 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በእግዚአብሔር ልጅ ማመን

1. ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፤ አባትንም የሚወድ ሁሉ ልጁንም እንደዚሁ ይወዳል።

2. እግዚአብሔርን ስንወድና ትእዛዛቱን ስንፈጽም የእግዚአብሔርን ልጆች እንደ ምንወድ በዚህ እናውቃለን፤

3. እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነውና። ትእዛዛቱም ከባድ አይደሉም፤

4. ምክንያቱም ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምን የሚያሸንፈውም እምነታችን ነው።

5. ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በስተቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማነው?

6. በውሃና በደም የመጣው ይህ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ በውሃና በደም እንጂ በውሃ ብቻ አልመጣም። የሚመሰክረውም መንፈስ ነው፤ መንፈስ እውነት ነውና።

7. ስለዚህ ሦስት ምስክሮች አሉት።

8. እነርሱም መንፈሱ፣ ውሃውና ደሙ ናቸው፤ ሦስቱም ይስማማሉ።

9. የሰውን ምስክርነት ከተቀበልን፣ የእግዚአብሔር ምስክርነት ከዚያም ይልቃል፤ ይህ ስለ ልጁ የሰጠው የእግዚአብሔር ምስክርነት ነውና።

10. በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን ሁሉ በልቡ ምስክር አለው፤ ማንም እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ እግዚአብሔር ስለ ልጁ የሰጠውን ምስክርነት ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።

11. ምስክርነቱም ይህ ነው፤ እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ሰጠን፤ ይህም ሕይወት ያለው በልጁ ነው።

12. ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።

ማጠቃለያ ሐሳብ

13. በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ እናንተ፣ የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ ይህን እጽፍላችኋለሁ፤

14. በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ያለን ድፍረት ይህ ነው፤ ማንኛውንም ነገር እንደ ፈቃዱ ብንለምን እርሱ ይሰማናል፤

15. የምንለምነውን ሁሉ እንደሚሰማን ካወቅን፣ የለመነውንም ነገር እንደ ተቀበልን እናውቃለን።

16. ማንም ሰው ወንድሙ ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይጸልይ፤ እግዚአብሔርም ለሞት የማያበቃ ኀጢአት ላደረጉት ሕይወትን ይሰጣል። ለሞት የሚያበቃም ኀጢአት አለ፤ ስለዚህኛው ግን ይጸልይ አልልም።

17. ዐመፅ ሁሉ ኀጢአት ነው፤ ለሞት የማያበቃም ኀጢአት አለ።

18. ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአት እንደማያደርግ ነገር ግን የእግዚአብሔር ልጅ እንደሚጠብቀው፣ ክፉውም እንደማይነካው እናውቃለን።

19. እኛ ከእግዚአብሔር እንደሆንን፣ መላው ዓለምም በክፉው ሥር እንደሆነ እናውቃለን።

20. የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እርሱን እንድናውቅ ማስተዋልን እንደ ሰጠን እናውቃለን፤ እኛም እውነተኛ በሆነው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለን። እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው።

21. ልጆች ሆይ፤ ራሳችሁን ከጣዖቶች ጠብቁ።