ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 2:3-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን።

4. “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።

5. ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤

6. ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7. ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው።

8. በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው።

9. በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ።

10. ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም።

11. ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

12. ልጆች ሆይ፤ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣እጽፍላችኋለሁ።

13. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

14. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ጽፍላችኋለሁ።

15. ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤

16. ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።

17. ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ዮሐንስ 2