ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4
  5. 5

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ዮሐንስ 2 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

2. እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም።

3. ትእዛዛቱን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን።

4. “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዙን የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም።

5. ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ ፍጹም ሆኖአል። በእርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤

6. ማንም በእርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል።

7. ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው።

8. በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው።

9. በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ።

10. ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም።

11. ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።

12. ልጆች ሆይ፤ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣እጽፍላችኋለሁ።

13. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።

14. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ጽፍላችኋለሁ።

ዓለምን አትውደዱ

15. ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤

16. ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።

17. ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።

ከክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጠንቀቅ

18. ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።

19. ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።

20. እናንተ ግን ከእርሱ ከቅዱሱ፣ ቅባት አላችሁና፤ ሁላችሁም እውነትን ታውቃላችሁ።

21. እኔ የምጽፍላችሁ እውነትን ስለማታውቁ አይደለም፤ ነገር ግን እውነትን ስለምታውቁትና ከእውነት ምንም ውሸት ስለማይወጣ ነው።

22. ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ሐሰተኛ ማነው? ይህ አብንና ወልድን የሚክደው የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።

23. ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ የለውም፤ ወልድን የሚያምን ሁሉ አብም አለው።

24. ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ይኑር፤ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ውስጥ ቢኖር፣ እናንተም በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።

25. ይህ እርሱ የሰጠን ተስፋ የዘላለም ሕይወት ነው።

26. ስለሚያስቷችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።

27. እናንተ ግን ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በውስጣችሁ ይኖራልና፤ ማንም እንዲያስተምራችሁ አያስፈልግም፤ ነገር ግን እውነት እንጂ ሐሰት ያልሆነው የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉም ነገር እንደሚያስተምራችሁ፣ ያም እውነት እንጂ ሐሰት እንዳልሆነ፣ እናንተንም እንዳስተማራችሁ በእርሱ ኑሩ።

የእግዚአብሔር ልጆች

28. እንግዲህ ልጆች ሆይ፤ እርሱ ሲገለጥ ድፍረት እንዲኖረን፣ በሚመጣበትም ጊዜ በፊቱ እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።

29. እርሱ ጻድቅ መሆኑን ካወቃችሁ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ ታውቃላችሁ።