ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ተሰሎንቄ 2:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ።

2. እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደር ስብንም እንኳ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን።

3. የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም።

4. ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት ብለን አይደለም።

5. የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው።

6. ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንባችሁ ነበር፤

7. ነገር ግን እናት ልጅዋን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን።

8. የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ።

9. ወንድሞች ሆይ፤ ጥረታችንንና ድካማችንን ታስታውሳላችሁ፤ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እየሠራን ወንጌል ሰበክንላችሁ።

10. በእናንተ በምታምኑት መካከል ሳለን እንዴት በቅድስና፣ በጽድቅ እንዲሁም ያለ ነቀፋ ሆነን እንደኖርን እናንተም እግዚአብሔርም ምስክሮች ናችሁ።

11. አባት ለገዛ ልጆቹ እንደሚሆን እኛም ለእያንዳንዳችሁ የቱን ያህል እንደሆንን ታውቃላችሁና፤

12. ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትኖሩ ዘንድ አበረታታናችሁ፤ አጽናናችሁ፤ አጥብቀንም ለመንናችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ተሰሎንቄ 2