ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 3:9-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።

10. ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ እንደ አንድ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልሁ፤ ሌላውም በላዩ ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት።

11. ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ሌላ መሠረት መጣል የሚችል ማንም የለም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

12. ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ወይም በብር፣ በከበረ ድንጋይ ወይም በዕንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣

13. ሥራው እንዴት እንደሆነ ይታያል፤ ምክንያቱም ያ ቀን ወደ ብርሃን ያመጣዋል። በእሳት ስለሚገለጥ እሳቱ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ምንነት ይፈትናል።

14. ማንም የገነባው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤

15. ሥራው የተቃጠለበት ግን ሽልማት ይቀርበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ይሁን እንጂ የሚድነው በእሳት ውስጥ በጭንቅ እንደሚያልፍ ሆኖ ነው።

16. እናንተ ራሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውስጣችሁ እንደሚኖር አታውቁምን?

17. ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፤ ያም ቤተ መቅደስ እናንተ ናችሁ።

18. ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፣ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ራሱን እንደ ሞኝ ይቍጠር።

19. የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “እርሱ ጥበበኞችን በራሳቸው ተንኰል ይይዛቸዋል፤”

20. በሌላ ስፍራ ደግሞ፣ “ጌታ የጥበበኞች ሐሳብ ከንቱ መሆኑን ያውቃል” ተብሎ ተጽፎአል፤

21. እንግዲህ ማንም በሰው አይመካ። ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፤

22. ጳውሎስም ሆነ አጵሎስ ወይም ኬፋ፣ ዓለምም ሆነ ሕይወት ወይም ሞት፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው፣ ሁሉ የእናንተ ነው፤

23. እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 3