ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 3:3-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ፤ ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን?

4. ምክንያቱም አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ቢል፣ ሰብአዊ ፍጡር ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?

5. ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው።

6. እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው።

7. ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም።

8. የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል።

9. እኛ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሠራ ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ።

10. ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ እንደ አንድ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልሁ፤ ሌላውም በላዩ ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት።

11. ምክንያቱም አንድ ጊዜ ከተመሠረተው መሠረት በቀር ሌላ መሠረት መጣል የሚችል ማንም የለም፤ ይህም መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

12. ማንም በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ወይም በብር፣ በከበረ ድንጋይ ወይም በዕንጨት፣ በሣር ወይም በአገዳ ቢያንጽ፣

13. ሥራው እንዴት እንደሆነ ይታያል፤ ምክንያቱም ያ ቀን ወደ ብርሃን ያመጣዋል። በእሳት ስለሚገለጥ እሳቱ የእያንዳንዱን ሰው ሥራ ምንነት ይፈትናል።

14. ማንም የገነባው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤

15. ሥራው የተቃጠለበት ግን ሽልማት ይቀርበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ይሁን እንጂ የሚድነው በእሳት ውስጥ በጭንቅ እንደሚያልፍ ሆኖ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 3