ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 16:5-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. በመቄዶንያ በኩል ማለፌ ስለማይቀር፣ መቄዶንያ ከደረስሁ በኋላ ወደ እናንተ እመጣለሁ።

6. ወደምሄድበት ወደ ማናቸውም ስፍራ በጒዞዬ እንድትረዱኝ፣ እናንተ ዘንድ እቈይ ይሆናል፤ ምናልባትም ክረምቱን ከእናንተ ጋር እሰነብት ይሆናል።

7. አሁን እግረ መንገዴን ሳልፍ ልጐበኛችሁ አልፈልግም፤ ጌታ ቢፈቅድ ረዘም ላለ ጊዜ እናንተ ዘንድ ለመሰንበት ተስፋ አደርጋለሁ።

8. ነገር ግን እስከ በዓለ ኀምሳ በኤፌሶን እቈያለሁ፤

9. ምክንያቱም ታላቅ የሥራ በር ተከፍቶልኛል፤ ብዙ ተቃዋሚዎችም አሉብኝ።

10. ጢሞቴዎስ ወደ እናንተ ከመጣ፣ አብሮአችሁ ያለ ፍርሀት እንዲቀመጥ አድርጉ፤ እርሱም እንደ እኔ የጌታን ሥራ የሚሠራ ነውና።

11. ስለዚህ ማንም አይናቀው፤ በሰላም ወደ እኔ እንዲመለስ ርዱት፤ መመለሱንም ከወንድሞች ጋር እየጠበቅን ነው።

12. ስለ ወንድማችን ስለ አጵሎስ ደግሞ፣ ከወንድሞች ጋር ወደ እናንተ እንዲመጣ አጥብቄ ለምኜው ነበር፤ እርሱ ግን አሁን ለመምጣት አልፈለገም፤ ሲመቸው ግን ይመጣል።

13. ንቁ፤ በእምነት ጽኑ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ፤

14. የምታደርጉትን ሁሉ በፍቅር አድርጉ።

15. የእስጢፋኖስ ቤተ ሰዎች በአካይያ የመጀመሪያዎቹ አማኞች እንደሆኑና ቅዱሳንንም ለማገልገል ራሳቸውን እንደ ሰጡ ታውቃላችሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ይህን እለምናችኋለሁ፤

16. እንደ እነርሱ ላሉትና ከእነርሱም ጋር በአገልግሎት ለሚደክሙ ሁሉ ታዘዙ።

17. እስጢፋኖስ፣ ፈርዶናጥስና አካይቆስ በመምጣታቸው ደስ ብሎኛል፤ ምክንያቱም እናንተ እዚህ ባለመኖራችሁ የጐደለኝን አሟልተዋል፤

18. የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋልና። ስለዚህ እንደነዚህ ያሉትን ሰዎች መታወቅ ይገባቸዋል።

19. በእስያ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። አቂላና ጵርስቅላ፣ በቤታቸውም ያለችው ቤተ ክርስቲያን የከበረ ሰላምታ በጌታ ያቀርቡላችኋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 16