ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

1 ቆሮንቶስ 11:22-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ለመሆኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በመናቅ፣ ምንም የሌላቸውን ታሳፍራላችሁን? እንግዲህ ምን ልበላችሁ? በዚህ ነገር ላመስግናችሁን? ፈጽሞ አላመሰግናችሁም።

23. እኔ ከጌታ የተቀበልሁትን ለእናንተ አስተላልፌአለሁና፤ ጌታ ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ሌሊት እንጀራን አንሥቶ

24. ከባረከ በኋላ ቈርሶ፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሆን ሥጋዬ ነው፤ ለመታሰቢያዬም አድርጉት” አለ።

25. እንዲሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፣ “ይህ ጽዋ በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው፤ ስለዚህ ከጽዋው በምትጠጡበት ጊዜ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

26. ይህን እንጀራ በምትበሉበት ጊዜ፣ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።

27. እንግዲህ ማንም ሳይገባው፣ ይህን እንጀራ ቢበላ ወይም የጌታን ጽዋ ቢጠጣ፣ የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ ይሆናል።

28. ማንም ሰው ከዚህ እንጀራ ከመብላቱና ከዚህ ጽዋ ከመጠጣቱ በፊት፣ ራሱን ይመርምር፤

29. ምክንያቱም ማንም የጌታን ሥጋ ሳይገባው ቢበላና ቢጠጣ ፍርድ የሚያመጣበትን ይበላል፤ ይጠጣል።

30. ከእናንተ መካከል ብዙዎች የደከሙትና የታመሙት፣ አንዳንዶችም ያንቀላፉት በዚህ ምክንያት ነው።

31. ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር።

32. ነገር ግን ጌታ በሚፈርድብን ጊዜ እንገሠጻለን፤ ይኸውም ከዓለም ጋር አብረን እንዳንኰነን ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 1 ቆሮንቶስ 11