ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 9:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የሜዶናዊው የአርጤክስስ ልጅ ዳርዮስ በባቢሎን በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት፣

2. በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ እኔ ዳንኤል ለነቢዩ ለኤርምያስ በተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ የኢየሩሳሌም መፈራረስ ሰባ ዓመት እንደሚቈይ ከቅዱሳት መጻሕፍት አስተዋልሁ።

3. ስለዚህ ማቅ ለብሼ፣ በራሴም ላይ ዐመድ ነስንሼ፣ በጾምና በጸሎት፣ በምልጃም ፊቴን ወደ ጌታ አምላክ አቀናሁ።

4. ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ተናዘዝሁም፤“ከሚወዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ሁሉ ጋር የፍቅር ቃል ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ ታላቅና የተፈራህ አምላክ፤ ጌታ ሆይ፤

5. እኛ ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናልም፤ ክፋትን አድርገናል፤ ዐምፀናልም፤ ከትእዛዝህና ከሕግህ ዘወር ብለናል።

6. ለንጉሦቻችን፣ ለልዑሎቻችንና ለአባቶቻችን እንዲሁም ለምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በአንተ ስም የተናገሩትን አገልጋዮችህን ነቢያትን አልሰማንም።

7. “ጌታ ሆይ፤ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ለአንተ ታማኞች ባለመሆናችን እኛን በበተንህባቸው አገሮች ሁሉ የምንገኝ የይሁዳ ሰዎች፣ የኢየሩሳሌምና የመላው እስራኤል ሕዝብ፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ያለን በዚህ ቀን በኀፍረት ተከናንበናል።

8. እግዚአብሔር ሆይ፤ እኛና ንጉሦቻችን፣ ልዑሎቻችንና አባቶቻችን በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን በኀፍረት ተከናንበናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 9