ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 8:16-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ከኡባልም፣ “ገብርኤል ሆይ፤ ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጒም ንገረው” ብሎ የሚጮኽ የሰው ድምፅ ሰማሁ።

17. እኔ ወደ ቆምሁበት ስፍራ እየቀረበ ሲመጣ፣ ደንግጬ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ራእዩ ስለ ዘመኑ ፍጻሜ እንደሆነ አስተውል” አለኝ።

18. እየተናገረኝ ሳለ፣ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ በከባድ እንቅልፍም ተዋጥሁ፤ እርሱ ግን ዳሰሰኝና በእግሮቼ አቆመኝ።

19. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “ራእዩ በመጨረሻው ዘመን ሊሆን ያለውን የሚያመለክት ስለ ሆነ፣ በኋላ በቊጣው ዘመን ምን እንደሚሆን እነግርሃለሁ፤

20. ያየኸው ሁለት ቀንዶች የነበሩት አውራ በግ፣ የሜዶንና የፋርስን መንግሥታት ያመለክታል።

21. ጠጒራሙ ፍየል የግሪክ ንጉሥ ሲሆን፣ በዐይኖቹም መካከል ያለው ትልቁ ቀንድ የመጀመሪያው ንጉሥ ነው።

22. የተሰበረውን ቀንድ የተኩት አራቱ ቀንዶች፣ ከመንግሥቱ የሚወጡትን አራት መንግሥታት ያመለክታሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም።

23. “በዘመነ መንግሥታቸው በስተ መጨረሻ፣ ዐመፀኞች ፍጹም እየከፉ በሚሄዱበት ጊዜ፣ አስፈሪ ፊት ያለው አታላይ ንጉሥ ይነሣል።

24. እጅግ ብርቱ ይሆናል፤ ነገር ግን በገዛ ኀይሉ አይደለም። አሠቃቂ ጥፋት ይፈጽማል፤ የሚያደርገው ሁሉ ይከናወንለታል፤ ኀያላን ሰዎችንና ቅዱሳኑን ሕዝብ ያጠፋል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 8