ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 6:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤

2. በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፤ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጒዳት እንዳይደርስበት፣ መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ።

3. ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው አሰበ።

4. በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ሊከሱት ሰበብ ፈለጉ፤ ነገር ግን አላገኙበትም፤ ዳንኤል ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለ ነበር፣ በእርሱ ላይ ስሕተት ሊያገኙ አልቻሉም።

5. እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋር በተያያዘ ጒዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ሰው የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ።

6. ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

7. ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ፣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፣ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል።

8. ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።”

9. ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 6