ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 5:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ነገር ግን ልቡ በትዕቢት በጸናና በእብሪት በተሞላ ጊዜ ከዙፋኑ ተወገደ፤ ክብሩም ተገፈፈ።

21. ከሰው መካከል ተሰደደ፤ የእንስሳም አእምሮ ተሰጠው፤ ከዱር አህዮች ጋር ኖረ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ፤ ልዑል አምላክ በሰዎች መንግሥታት ላይ እንደሚገዛና እነርሱንም ለወደደው እንደሚሰጥ እስኪያውቅ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

22. “ቤልሻዛር ሆይ፤ አንተ ልጁ ሆነህ ይህን ሁሉ ብታውቅም፣ ራስህን ዝቅ አላደረግህም፤

23. ይልቁንም በሰማይ አምላክ ላይ በመታበይ፣ ራስህን ከፍ ከፍ አደረግህ፤ የመቅደሱን መጠጫዎች አስመጣህ፤ አንተና መኳንንትህ፣ ሚስቶችህና ቍባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ማየት፣ መስማት፣ ማስተዋልም የማይችሉትን የብርና የወርቅ፣ የናስና የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገንህ። ሕይወትህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ ግን አላከበርህም።

24. ስለዚህ እርሱ ጽሕፈቱን የጻፈውን እጅ ላከ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 5