ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 5:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ቤልሻዛር የወይን ጠጁን እየጠጣ ሳለ፣ አባቱ ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ያመጣቸውን የወርቅና የብር መጠጫዎችን እርሱና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ እንዲያመጡለት አዘዘ።

3. ከዚያም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተወሰዱትን የወርቅ መጠጫዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቱ፣ ሚስቶቹና ቍባቶቹም ጠጡባቸው።

4. የወይን ጠጁንም እየጠጡ የወርቅና የብር፣ የናስ፣ የብረት፣ የዕንጨትና የድንጋይ አማልክትን አመሰገኑ።

5. በድንገትም የሰው እጅ ጣቶች ታዩ፤ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በመቅረዙ ትይዩ ባለው ግድግዳ ልስን ላይ ጻፉ፤ ንጉሡም ይጽፍ የነበረውን እጅ አየ፤

6. በዚያን ጊዜ ንጉሡ በድንጋጤ ተሞላ፤ ፊቱም ተለዋወጠ፤ እጆቹና እግሮቹ ከዱት፤ ጒልበቶቹም ተብረከረኩ።

7. ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ አስማተኞችን፣ ኮከብ ቈጣሪዎችንና መተተኞችን እንዲያስገቡለት አዘዘ፤ ለባቢሎናውያኑ ጠቢባን እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ጽሕፈት አንብቦ ትርጒሙን የሚነግረኝን ሐምራዊ መጐናጸፊያ አለብሰዋለሁ፤ የወርቅ ሐብልም በዐንገቱ ላይ አጠልቅለታለሁ፤ በመንግሥቴም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል።”

8. ከዚያም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ሊያነብም ሆነ ትርጒሙ ምን እንደሆነ ለንጉሡ ሊነግር የሚችል ማንም አልነበረም።

9. ንጉሥ ቤልሻዛር ከፊት ይልቅ ፈራ፤ ፊቱም እጅግ ተለወጠ፤ መኳንንቱም ግራ ገብቶአቸው ተደናገጡ።

10. ንግሥቲቱም የንጉሡንና የመኳንንቱን ድምፅ ሰምታ ወደ ግብዣው አዳራሽ ገባች፤ እንዲህም አለች፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ፤ አትደንግጥ፤ ፊትህም አይለዋወጥ!

11. በመንግሥትህ ውስጥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት አንድ ሰው አለ፤ ይህ ሰው በአባትህ ዘመን እንደ አማልክት ጥበብና ማስተዋል፣ ዕውቀትም የሞላበት ሆኖ ተገኝቶአል፤ አባትህ ንጉሥ ናቡከደነፆርም የጠንቋዮች፣ የአስማተኞች፣ የኮከብ ቈጣሪዎችና የመተተኞች አለቃ አደረገው።

12. ንጉሡ ብልጣሶር ብሎ የጠራው ይህ ዳንኤል መልካም መንፈስ፣ ዕውቀትና ማስተዋል ያለው ሆኖ ተገኘ፤ ሕልምን የመተርጐም፣ እንቆቅልሽን የመፍታትና የተሰወረውን የመግለጥ ልዩ ችሎታም ነበረው። ስለዚህ ዳንኤልን አስጠራ፤ እርሱም የጽሕፈቱን ትርጒም ይነግርሃል።”

13. ዳንኤልንም ወደ ንጉሡ አቀረቡት፤ ንጉሡም እንዲህ አለው፤ “ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ማርኮ ካመጣቸው መካከል አንዱ የሆንኸው ዳንኤል አንተ ነህን?

14. የአማልክት መንፈስ በውስጥህ እንዳለ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋልና ልዩ ጥበብ እንዳለህ ሰምቻለሁ፤

15. ይህን ጽሕፈት አንብበው ትርጒሙ ምን እንደሆነ ይነግሩኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች በፊቴ ቀርበው ነበር፤ ነገር ግን ሊገልጡት አልቻሉም።

16. አንተ ግን መተርጐምና አስቸጋሪ የሆነውን ነገር መፍታት እንደምትችል ሰምቻለሁ። ይህን ጽሕፈት አንብበህ ትርጒሙን ብትነግረኝ፣ ሐምራዊ መጐናጸፊያ ያለብሱሃል፤ የወርቅ ሐብል በዐንገትህ ያጠልቁልሃል፤ የመንግሥት ሦስተኛ ገዥም ትደረጋለህ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 5