ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 3:6-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”

7. ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ።

8. በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤

9. ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

10. ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤

11. ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

12. ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”

13. ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤

14. ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው?

15. አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእምቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”

16. ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም።

17. ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።

18. ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”

19. ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድ አዘዘ፤

20. ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ።

21. እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 3