ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 2:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ንጉሡም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “እኔ ምን ብዬ እንደ ወሰንሁ ስለምታውቁ፣ ጊዜ ለማራዘም እንደምትሞክሩ ተረድቼአለሁ፤

9. ሕልሙን ባትነግሩኝ፣ አንድ ቅጣት ይጠብቃችኋል፤ ሁኔታው ይለወጣል ብላችሁ በማሰብ የሚያሳስቱ ነገሮችንና ክፉ ሐሳቦችን ልትነግሩኝ አሲራችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፤ ትርጒሙንም ልትነግሩኝ እንደምትችሉ በዚህ ዐውቃለሁ።”

10. ኮከብ ቈጣሪዎቹም ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ንጉሡ የጠየቀውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችል ሰው በምድር ላይ አይገኝም! ማንም ንጉሥ ምንም ያህል ታላቅና ኀያል ቢሆን፣ እንዲህ ዐይነት ነገር ማንኛውንም ጠንቋይ፣ አስማተኛ ወይም ኮከብ ቈጣሪን ጠይቆ ዐያውቅም።

11. ንጉሡ የሚጠይቀው እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፤ በሰዎች መካከል ከማይኖሩት ከአማልክት በቀር ለንጉሡ የሚገልጽለት የለም።”

12. ይህም ንጉሡን እጅግ አበሳጨው፤ አስቈጣውም፤ በባቢሎን ያሉ ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም አዘዘ፤

13. ጠቢባን ሁሉ እንዲገደሉም ዐዋጅ ወጣ፤ ዳንኤልንና ጓደኞቹን ፈልገው እንዲገድሉ ሰዎች ተላኩ።

14. የንጉሡ ዘበኞች አለቃ አርዮክ፣ የባቢሎንን ጠቢባን ለመግደል በመጣ ጊዜ፣ ዳንኤል በጥበብና በዘዴ አነጋገረው።

15. የንጉሡን መኰንን፣ “ንጉሡ እንዲህ ዐይነት ከባድ ዐዋጅ ያወጣው ስለ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቀው፤ አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል ገለጠለት።

16. በዚህን ጊዜ፣ ዳንኤልም ገብቶ ሕልሙን ይተረጒምለት ዘንድ ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።

17. ከዚህ በኋላ ዳንኤል ወደ ቤቱ ተመልሶ ለጓደኞቹ ለአናንያ፣ ለሚሳኤልና ለአዛርያ ነገሩን ገለጠላቸው።

18. እርሱና ጓደኞቹ ከቀሩት የባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይገደሉ፣ የሰማይ አምላክ ምሕረት ያደርግላቸውና ምስጢሩንም ይገልጥላቸው ዘንድ እንዲጸልዩ አሳሰባቸው።

19. ለዳንኤልም ምስጢሩ በሌሊት በራእይ ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ፤

20. እንዲህም አለ፤“ጥበብና ኀይል የእርሱ ነውና፣ የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ።

21. ጊዜንና ወቅትን ይለውጣል፤ነገሥታትን በዙፋን ያስቀምጣል፣ደግሞም ያወርዳቸዋል፤ጥበብን ለጠቢባን፣ዕውቀትንም ለሚያስተውሉ ይሰጣል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 2