ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 2:30-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ይህ ምስጢር ለእኔ የተገለጠው፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ ታላቅ ጥበብ ስላለኝ አይደለም፤ ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ አንተ ትርጒሙን እንድታውቅና በአእምሮህ ታሰላስለው የነበረው ነገር ምን እንደሆነ ትረዳ ዘንድ ነው።

31. “ንጉሥ ሆይ፤ በፊት ለፊትህ ግዙፍ የሆነ፣ የሚያብረቀርቅና የሚያስፈራ ታላቅ ምስል ቆሞ አየህ፤

32. የምስሉ ራስ ከንጹሕ ወርቅ፣ ደረቱና ክንዶቹ ከብር፣ ሆዱና ጭኖቹ ከናስ የተሠሩ ነበሩ፤

33. ቅልጥሞቹም ከብረት፣ እግሮቹም ከፊሉ ከብረት፣ ከፊሉም ከሸክላ የተሠሩ ነበሩ።

34. ይህን በመመልከት ላይ ሳለህ፣ አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም።

35. ወዲያውኑም ብረቱ፣ ሸክላው፣ ናሱ፣ ብሩና ወርቁ ተሰባበሩ፤ በበጋ ወራት በዐውድማ ላይ እንደሚገኝ እብቅም ሆኑ፤ ነፋስም አንዳች ሳያስቀር ጠራረጋቸው፤ ምስሉን የመታው ድንጋይ ግን ታላቅ ተራራ ሆነ፤ ምድርንም ሞላ።

36. “ሕልሙ ይህ ነበር፤ አሁን ትርጒሙን ለንጉሥ እንናገራለን።

37. ንጉሥ ሆይ፤ አንተ የነገሥታት ንጉሥ ነህ፤ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ሥልጣንን፣ ኀይልንና ክብርን ሰጥቶሃል፤

38. የሰው ልጆችን፣ የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፤ በየትም ቦታ ቢሆኑ፣ በሁሉም ላይ ገዥ አድርጎሃል፤ እንግዲህ የወርቁ ራስ አንተ ነህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 2