ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:37-45 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

37. ሴቶች ለሚወዱትም ሆነ ለአባቶቹ አማልክት ክብርን አይሰጥም፤ ማንኛውንም አምላክ አያከብርም፤ ነገር ግን ራሱን ከእነዚህ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል።

38. በእነርሱም ምትክ የምሽጎችን አምላክ ያከብራል፤ አባቶች የማያውቁትን አምላክ በወርቅ፣ በብር፣ በከበሩ ድንጋዮችና በውድ ስጦታዎች ያከብራል።

39. በባዕድ አምላክ ርዳታ ጽኑ ምሽጎችን ይወጋል፤ ለእርሱ የሚገዙትን በእጅጉ ያከብራቸዋል፤ በብዙ ሕዝብ ላይ ገዦች ያደርጋቸዋል፤ ምድሩንም በዋጋ ያከፋፍላቸዋል።

40. “በመጨረሻው ዘመን የደቡብ ንጉሥ ጦርነት ያውጅበታል፤ የሰሜን ንጉሥም በፈረሰኞችና በሠረገሎች፣ በብዙ መርከቦችም እንደ ማዕበል ይመጣበታል፤ ብዙ አገሮችን ይወራል፤ እንደ ጐርፍም እየጠራረገ በመካከላቸው ያልፋል።

41. መልካሚቱንም ምድር ይወራል፤ ብዙ አገሮች በእጁ ይወድቃሉ፤ ኤዶም፣ ሞዓብና የአሞን መሪዎች ግን ከእጁ ያመልጣሉ።

42. ሥልጣኑን በብዙ አገሮች ላይ ያንሰራፋል፤ ግብፅም አታመልጥም።

43. የወርቅና የብር ክምችትን፣ እንዲሁም የግብፅን ሀብት ሁሉ በቊጥጥሩ ሥር ያደርጋል፤ የሊቢያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይገዙለታል።

44. ነገር ግን ከምሥራቅና ከሰሜን የሚመጣ ወሬ ያስደነግጠዋል፤ ብዙዎችንም ለማጥፋትና ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል።

45. ንጉሣዊ ድንኳኖቹን በባሕሮች መካከል ውብ በሆነው ቅዱስ ተራራ ላይ ይተክላል፤ ይሁን እንጂ ወደ ፍጻሜው ይመጣል፤ ማንም አይረዳውም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11