ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:27-36 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

27. ልባቸው ወደ ክፋት ያዘነበለው ሁለቱ ነገሥታት፣ በአንድ ገበታ አብረው ይቀመጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ሐሰትን ይነጋገራሉ፤ ነገር ግን የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ አይከናወንላቸውም።

28. የሰሜን ንጉሥ ብዙ ሀብት ይዞ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ ነገር ግን ልቡ በተቀደሰው ኪዳን ላይ ይነሣሣል፤ ክፉ ነገርም ያደርግበታል፤ ከዚያም ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

29. “በተወሰነው ጊዜ ደቡቡን እንደ ገና ይወራል፤ በዚህ ጊዜ ግን ውጤቱ ከበፊቱ የተለየ ይሆናል።

30. የኪቲም መርከቦች ይቃወሙታል፤ ልቡም ይሸበራል። ወደ ኋላም ይመለሳል፤ ቊጣውን በተቀደሰው ኪዳን ላይ ያወርዳል፤ ተመልሶም የተቀደሰውን ኪዳን የተውትን ይንከባከባል።

31. “የጦር ሰራዊቶቹም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ በዚያም ጥፋትን የሚያመጣውን የጥፋት ርኵሰት ይተክላሉ፤

32. ኪዳኑን የሚተላለፉትን በማታለል ያስታል፤ አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ እርምጃም ይወስዳሉ።

33. “ለጊዜው በሰይፍ ቢወድቁም፣ ቢቃጠሉም፣ ቢማረኩና ቢዘረፉም፣ ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ብዙዎችን ያስተምራሉ።

34. በሚወድቁበት ጊዜ መጠነኛ ርዳታ ያገኛሉ፤ እውነተኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችም ይተባበሯቸዋል።

35. ጥበበኛ ከሆኑ ሰዎች አንዳንዶቹ ይሰናከላሉ፤ ይህም እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የጠሩ፣ የነጠሩና እንከን የሌለባቸው ይሆኑ ዘንድ ነው፤ የተወሰነው ጊዜ ገና አልደረሰምና።

36. “ንጉሡ ደስ እንዳለው ያደርጋል፤ ከአማልክት ሁሉ በላይ ራሱን እጅግ ከፍ በማድረግ በአማልክት አምላክ ላይ ተሰምቶ የማይታወቅ የስድብ ቃል ይናገራል፤ የቊጣውም ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ይሳካለታል፤ የተወሰነው ነገር ሁሉ መሆን አለበትና።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11