ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:21-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. “በእርሱም ፋንታ የተናቀ ሰው ይነግሣል፤ ንጉሣዊ ክብርም አይሰጠውም፤ ሕዝቡ በሰላም ተቀምጦ ሳለ በተንኰል መንግሥቱን ይይዛል።

22. ከፊቱ የሚቆመውን ታላቅ ሰራዊት፣ የቃል ኪዳኑንም አለቃ ሳይቀር ይደመስሳል።

23. ከእርሱ ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ የማታለል ሥራውን ይሠራል፤ ከጥቂት ሰዎች ጋር ለሥልጣን ይበቃል።

24. የበለጸጉትን ክፍለ አገሮች በሰላም ሳሉ በድንገት ይወርራቸዋል፤ አባቶቹም ሆኑ አያቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል፤ ይከናወንለታልም፤ ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለተከታዮቹ ያካፍላቸዋል፤ ምሽጎችን ለመጣል ያሤራል፤ ይህን የሚያደርገውም ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።

25. “ታላቅ ሰራዊት አደራጅቶ ኀይሉንና ብርታቱን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያነሣሣል፤ የደቡብ ንጉሥም ቊጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ ኀያል ሰራዊት ይዞ ጦርነትን ያውጃል፤ ነገር ግን ከተዶለተበት ሤራ የተነሣ መቋቋም አይችልም።

26. ከንጉሥ ማዕድ አብረውት ሲበሉ የነበሩት ሊያጠፉት ያሤራሉ፤ ሰራዊቱም ይደመሰሳል፤ ብዙዎቹም በጦርነት ይወድቃሉ።

27. ልባቸው ወደ ክፋት ያዘነበለው ሁለቱ ነገሥታት፣ በአንድ ገበታ አብረው ይቀመጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ሐሰትን ይነጋገራሉ፤ ነገር ግን የተወሰነው ጊዜ ገና ስለ ሆነ አይከናወንላቸውም።

28. የሰሜን ንጉሥ ብዙ ሀብት ይዞ ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል፤ ነገር ግን ልቡ በተቀደሰው ኪዳን ላይ ይነሣሣል፤ ክፉ ነገርም ያደርግበታል፤ ከዚያም ወደ ገዛ አገሩ ይመለሳል።

29. “በተወሰነው ጊዜ ደቡቡን እንደ ገና ይወራል፤ በዚህ ጊዜ ግን ውጤቱ ከበፊቱ የተለየ ይሆናል።

30. የኪቲም መርከቦች ይቃወሙታል፤ ልቡም ይሸበራል። ወደ ኋላም ይመለሳል፤ ቊጣውን በተቀደሰው ኪዳን ላይ ያወርዳል፤ ተመልሶም የተቀደሰውን ኪዳን የተውትን ይንከባከባል።

31. “የጦር ሰራዊቶቹም ቤተ መቅደሱንና ቅጥሩን ያረክሳሉ፤ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፤ በዚያም ጥፋትን የሚያመጣውን የጥፋት ርኵሰት ይተክላሉ፤

32. ኪዳኑን የሚተላለፉትን በማታለል ያስታል፤ አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ግን ጸንተው ይቃወሙታል፤ እርምጃም ይወስዳሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11