ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዳንኤል 11:17-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. በመንግሥቱ ያለውን ሰራዊት ሁሉ ይዞ ለመምጣት ይወስናል፤ ከደቡብም ንጉሥ ጋር ይስማማል፤ ይህንም መንግሥት ለመጣል ሴት ልጁን ይድርለታል፤ ይሁን እንጂ ዕቅዱ አይሳካለትም፤ ያሰበውም ነገር አይጠቅመውም።

18. ከዚህም በኋላ በባሕር ጠረፍ ወዳሉት አገሮች ፊቱን በመመለስ ብዙዎቹን ይይዛል፤ ነገር ግን አንድ አዛዥ ትዕቢቱን ያከሽፍበታል፤ በራሱም ላይ ይመልስበታል።

19. በገዛ አገሩ ወዳሉት ምሽጎችም ፊቱን ይመልሳል፤ ነገር ግን ተሰናክሎ ይወድቃል፤ ዳግምም አይታይም።

20. “በእርሱ ቦታ የሚተካውም የመንግሥቱን ክብር ለማስጠበቅ ግብር አስገባሪ ይልካል፤ ይሁን እንጂ በቊጣ ወይም በጦርነት ሳይሆን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይገደላል።

21. “በእርሱም ፋንታ የተናቀ ሰው ይነግሣል፤ ንጉሣዊ ክብርም አይሰጠውም፤ ሕዝቡ በሰላም ተቀምጦ ሳለ በተንኰል መንግሥቱን ይይዛል።

22. ከፊቱ የሚቆመውን ታላቅ ሰራዊት፣ የቃል ኪዳኑንም አለቃ ሳይቀር ይደመስሳል።

23. ከእርሱ ጋር ስምምነት ከተደረገ በኋላ የማታለል ሥራውን ይሠራል፤ ከጥቂት ሰዎች ጋር ለሥልጣን ይበቃል።

24. የበለጸጉትን ክፍለ አገሮች በሰላም ሳሉ በድንገት ይወርራቸዋል፤ አባቶቹም ሆኑ አያቶቹ ያላደረጉትን ነገር ያደርጋል፤ ይከናወንለታልም፤ ብዝበዛውን፣ ምርኮውንና የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለተከታዮቹ ያካፍላቸዋል፤ ምሽጎችን ለመጣል ያሤራል፤ ይህን የሚያደርገውም ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዳንኤል 11