ምዕራፎች

  1. 1
  2. 2
  3. 3
  4. 4

ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዮናስ 3 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዮናስ ወደ ነነዌ ሄደ

1. የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤

2. “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።”

3. ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ። በዚህ ጊዜ ነነዌ ታላቅ ከተማ ነበረች፤ እርሷንም ከዳር እስከ ዳር ለመጐብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር።

4. ዮናስም ወደ ከተማዪቱ ገብቶ የመጀመሪያውን ቀን ከተጓዘ በኋላ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” ብሎ ዐወጀ።

5. የነነዌም ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ፤ ጾምንም ዐወጁ፤ ሰዎቹም ሁሉ ከትልቁ እስከ ትንሹ ማቅ ለበሱ።

6. ወሬውም ወደ ነነዌ ንጉሥ በደረሰ ጊዜ፣ ከዙፋኑ ወረደ፤ ልብሱንም አወለቀ፤ ማቅም ለብሶ በዐመድ ላይ ተቀመጠ።

7. ከዚያም እንዲህ ሲል በነነዌ ዐዋጅ አስነገረ፤“ከንጉሡና ከመሳፍንቱ የወጣ ዐዋጅ፤ማንም ሰው ወይም እንስሳ፣ የከብት መንጋም ሆነ የበግ መንጋ፣ ምንም ነገር አይቅመስ፤ አይብላ፤ ውሃም አይጠጣ።

8. ነገር ግን ሰውም እንስሳም ማቅ ይልበስ፤ ሁሉም አጥብቆ ወደ እግዚአብሔር ይጩኽ፤ ሰዎችም ሁሉ ክፉ መንገዳቸውንና የግፍ ሥራቸውን ይተዉ።

9. እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ራርቶ ከጽኑ ቍጣው ይመለስም እንደሆነ ማን ያውቃል?”

10. እግዚአብሔርም ምን እንዳደረጉና ከክፉ መንገዳቸውም እንዴት እንደ ተመለሱ ባየ ጊዜ ራራላቸው፤ በእነርሱም ላይ ሊያመጣ ያሰበውን ጥፋት አላደረገም።