ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 7:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ኖኅ በተወለደ በ600ኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤

12. አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ።

13. በዚያኑ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ።

14. ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ አብረዋቸው ገቡ።

15. የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጡራን በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ።

16. ከሕያዋንም ፍጡራን ሁሉ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ከውጭ ዘጋበት።

17. የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት።

18. ውሃው በምድር ላይ በጣም እየ ጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች።

19. ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው።

20. ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ 7 ሜትር ያህል ከፍ አለ።

21. በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጡራን፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ።

22. በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጡራን ሁሉ ሞቱ።

23. ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።

24. ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቈየ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 7