ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 6:10-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።

11. ምድር በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች።

12. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ፤ እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና

13. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በእርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ።

14. አንተ ግን በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው።

15. እንዲህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ 140 ሜትር፣ ወርዷ 23 ሜትር፣ ከፍታዋ 13.5 ሜትር ይሁን።

16. ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለ ሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት።

17. እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል።

18. ካንተ ጋር ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ።

19. ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ።

20. ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ።

21. ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 6