ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 47:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው።

2. ከወንድሞቹም መካከል አምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው።

3. ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁ ምንድ ነው?” ሲል ጠየቃቸው።እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት፤

4. ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት።

5. ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤

6. የግብፅ ምድር እንደሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኀላፊዎች አድርጋቸው።”

7. ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አግብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብ ፈርዖንን ከመረቀው በኋላ

8. ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው።

9. ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍኩት ዘመን 130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋር ሲነጻጸር አጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት።

10. ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ።

11. ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብፅ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 47