ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 45:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር መጨዋወት ጀመሩ።

16. የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው።

17. ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ።

18. ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብፅ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሎአችሁ ትኖራላችሁ።’

19. “ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብፅ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጉዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ።

20. ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፣ ከግብፅ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ”

21. የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው።

22. ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና አምስት የክት ልብስ ሰጠው።

23. ለአባቱም በግብፅ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት።

24. ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከእርሱም ሲሰናበቱ፣ መንገድ ላይ እንዳትጣሉ” አላቸው።

25. እነርሱም ከግብፅ ወጥተው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ።

26. አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብፅ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኖአል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም።

27. ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብፅ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ።

28. ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 45