ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 44:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፣ ልክ እንደ ተባለው ተናገራቸው።

7. እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም።

8. ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን?

9. የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።”

10. እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው።

11. እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ።

12. ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፣ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ።

13. በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ።

14. ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ።

15. ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው።

16. ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጦአል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ።

17. ዮሴፍም፣ “ይህንንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው።

18. ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖን ያህል የተከበርህ ስለ ሆንህ፣ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ።

19. ጌታዬ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቈ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 44