ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 44:26-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን አብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በስተቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው።

27. “አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤

28. አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፣ “በእርግጥ የአውሬ እራት ሆኖአል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቶአል።

29. አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጒዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’

30. “እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፣ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፣

31. የልጁን ከእኛ ጋር አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን።

32. እኔ አገልጋይ፣ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፣ ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቍጠረኝ’ በማለት፣ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ።

33. “ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋር ይመለስ።

34. ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 44