ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 42:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፣ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቍጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፣ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት።

8. ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም።

9. በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።

10. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤

11. ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።”

12. እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፤ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።

13. እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፣ አንዱ ግን የለም” አሉት።

14. ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ!

15. ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው።

16. በሉ፣ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፣ እስር ቤት ትቈያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፣ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው።

17. ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው።

18. በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 42