ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 42:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ፣ ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ለምን እርስ በርስ ትተያያላችሁ?

2. በግብፅ እህል መኖሩን ሰምቻለሁ፤ ስለዚህ ከመሞት መሰንበት ይሻላልና ወደዚያው ወርዳችሁ እህል ሸምቱልን” አላቸው።

3. ከዚያም ዐሥሩ የዮሴፍ ወንድሞች እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ወረዱ።

4. ነገር ግን ያዕቆብ የዮሴፍን ወንድም ብንያምን፣ ክፉ ነገር ይደርስበታል በሚል ፍርሀት ከወንድሞቹ ጋር አላከውም።

5. ራቡ በከነዓንም በመበርታቱ፣ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ከሄዱት ሰዎች መካከል የእስራኤል ልጆችም ነበሩ።

6. በዚህ ጊዜ ዮሴፍ የምድሪቱ ገዥ ነበር፤ ለአገሩ ሰዎች ሁሉ እህል የሚሸጥላቸው እርሱ ነበር። የዮሴፍ ወንድሞችም እንደ ደረሱ፣ ከፊቱ ቀርበው ወደ ምድር ለጥ ብለው እጅ ነሡት።

7. ዮሴፍም ወንድሞቹን ገና ሲያያቸው ወዲያውኑ ዐወቃቸው፤ ነገር ግን እንደማያውቃቸው ሆኖ፣ “ከየት የመጣችሁ ናችሁ?” ብሎ በቍጣ ቃል ተናገራቸው። እነርሱም፣ “እህል፤ ለመሸመት ከከነዓን ምድር የመጣን ነን” ብለው መለሱለት።

8. ዮሴፍ ወንድሞቹን ቢያውቃቸውም እንኳ እነርሱ ግን አላወቁትም።

9. በዚህ ጊዜ ስለ ወንድሞቹ ያየው ሕልም ትዝ አለውና፣ “ሰላዮች ናችሁ፤ የመጣችሁት አገራችን በየትኛው በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።

10. እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ፤ እንዲህስ አይደለም፤ አገልጋዮችህ የመጣነው እህል ለመሸመት ነው፤

11. ሁላችንም የአንድ አባት ልጆች ነን፤ አገልጋዮችህ የታመንን ሰዎች እንጂ ሰላዮች አይደለንም።”

12. እርሱም መልሶ፣ “አይደለም፤ በየት በኩል ለጥቃት የተጋለጠች መሆኗን ለመሰለል ነው” አላቸው።

13. እነርሱ ግን መልሰው፣ “እኛ አገልጋዮችህ በከነዓን አገር ከሚኖር ከአንድ ሰው የተወለድን ዐሥራ ሁለት ወንድማማቾች ነን። ትንሹ ወንድማችን አባታችን ዘንድ ሲሆን፣ አንዱ ግን የለም” አሉት።

14. ዮሴፍም እንዲህ አላቸው፤ “ነገርኋችሁ እኮ፤ ሰላዮች ናችሁ!

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 42