ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 41:36-47 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

36. የሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።”

37. ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት።

38. ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው።

39. ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንዳንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም።

40. አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”

41. ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን “በመላዪቱ የግብፅ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው።

42. ፈርዖንም ባለማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት።

43. በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፣ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው። ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው።

44. ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብፅ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው።

45. ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብፅ ምድር ተዘዋወረ።

46. ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ።

47. በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 41