ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 39:8-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።

9. በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?”

10. ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጒተውም፣ አልሰማትም፤ ከእርሷ ጋር መተኛቱ ይቅርና አብሯትም መሆን አልፈቀደም።

11. አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም።

12. እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል አብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።

13. እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣

14. የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሮአል! እዚህ ድረስ ሰተት ብሎ ገብቶ ካልተኛሁሽ አለኝ፤ እኔም ጩኸቴን ለቀቅሁት፤

15. ለእርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን ከአጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ።”

16. ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቆየችው።

17. ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤

18. ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።”

19. ጌታውም “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ፣ ተቈጣ።

20. ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው።

21. ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት ባለበት ጊዜ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፣ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 39