ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 33:12-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ዔሳውም “በል ተነሥና ጒዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው።

13. ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ።

14. ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጒዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።”

15. ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው።ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው።

16. ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ።

17. ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ።

18. ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ በከነዓን ወዳለችው ወደ ሴኬም በደኅና ደረሰ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ።

19. ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ ከኤሞር ልጆች በመቶ ጥሬ ብር ገዛ፤ ኤሞርም የሴኬም አባት ነበር።

20. በዚያም መሠዊያ አቁሞ፣ ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 33