ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 32:18-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. ‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተ ኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው፣”

19. እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎችን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤

20. በተለይም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለትን አትዘንጉ።” ይህንም ያዘዘው፣ “ዔሳው ከእኔ ጋር ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል” ብሎ ስላሰበ ነበር።

21. ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከእርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩበት ቦታ አደረ።

22. በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ።

23. ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ።

24. ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው አደረ።

25. ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብ ግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ።

26. በዚያን ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለ ሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው።ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።

27. ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው።እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ።

28. ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው።

29. ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው።ሰውዬውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው።

30. ስለዚህ ያዕቆብ፣ “እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው።

31. ጵኒኤልንም እንዳለፈ ፀሓይ ወጣችበት፤ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።

32. ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሹልዳን ከጭኑ ጋር የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም በጭኑ መጋጠሚያ ላይ ያለው የያዕቆብ ሹልዳ ተነክቶ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 32