ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:39-54 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

39. አውሬ የሰበረውንም ቢሆን እተካ ነበር እንጂ፣ ትራፊውን ለምልክትነት አምጥቼ አላውቅም፤ በቀንም ሆነ በሌሊት የተሰረቁትን ሁሉ ስታስከፍለኝ ኖረሃል።

40. ቀን በሐሩር ሌሊት በቊር ተቃጠልሁ፤ እንቅልፍም በዐይኔ አልዞር አለ፤

41. ሃያ ዓመት በቤትህ የኖርሁት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ዐሥራ አራት ዓመት ለሁለቱ ልጆችህ ብዬ አገለገልሁ፤ ስድስት ዓመት ስለ መንጋዎችህ ስል አገለገልሁ፤ ይህም ሆኖ ደመወዜን ዐሥር ጊዜ ለዋውጠኽብኛል።

42. የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም)፣ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅም ፍርሀት ከእኔ ጋር ባይሆን ኖሮ ባዶ እጄን ሰድደኸኝ ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን መከራዬን አይቶ፣ ልፋቴን ተመልክቶ ትናንት ሌሊት ገሠጸህ።”

43. ላባም ለያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶቹም፣ ልጆቹም የእኔው ልጆች ናቸው፣ መንጎቹም ቢሆኑ የራሴ ናቸው። ታዲያ፣ በእነዚህ ሴቶች ልጆቼና በወለዷቸው ልጆቻቸው ላይ ዛሬ ምን ማድረግ እችላለሁ?

44. በል አሁን ቃል ኪዳን እንጋባ፤ ኪዳኑም በአንተና በእኔ መካከል ምስክር ይሁን።”

45. ያዕቆብም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፤

46. ከዚያም ዘመዶቹን፣ “ድንጋይ ሰብስቡ” አላቸው። እነርሱም ድንጋይ እያመጡ ከመሩ፤ በክምሩም አጠገብ ምግብ በሉ።

47. ላባም ክምር ድንጋዩን ይጋርሠሀዱታ ብሎ ጠራው፤ ያዕቆብ ደግሞ ገለዓድ አለው።

48. ላባም “ይህ ክምር ድንጋይ በእኔና በአንተ መካከል ዛሬ ምስክር ነው” አለው። ጋልዒድ ተብሎ የተጠራውም በዚሁ ምክንያት ነው፤

49. ደግሞም ምጽጳ ተባለ፤ ምክንያቱም ላባ እንዲህ ብሎአልና፤

50. “ልጆቼን ብትበድላቸው ወይም ሌሎች ሚስቶች በላያቸው ላይ ብታገባ፣ ማንም ከእኛ ጋር ባይኖርም እንኳ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በአንተና በእኔ መካከል ምስክር መሆኑን አትርሳ።”

51. ደግሞም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ክምር ድንጋዩ እነሆ፤ በአንተና በእኔ መካከል ያቆምሁትም ሐውልት እነሆ፤

52. ይህን ክምር ድንጋይ አልፌ አንተን ለማጥቃት ላልመጣ፣ አንተም ይህን ክምር ድንጋይና ይህን ሐውልት አልፈህ እኔን ለማጥቃት ላትመጣ፣ ይህ ክምር ድንጋይ ምስክር ነው፤ ይህም ሐውልት ምስክር ነው።

53. የአብርሃም አምላክ፣ የናኮር አምላክ፣ የአባታቸውም አምላክ (ኤሎሂም) በመካከላችን ይፍረድብን”።ስለዚህ ያዕቆብ በአባቱ በይስሐቅ ፍርሀት ማለ።

54. ያዕቆብ በኰረብታማው አገር ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ዘመዶቹንም ምግብ እንዲበሉ ጋበዛቸው፤ እነርሱም ከበሉ በኋላ እዚያው አደሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31