ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:22-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. የያዕቆብ መኰብለል ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው።

23. ላባ ዘመዶቹን ይዞ ተነሣ፤ ያዕቆብንም ሰባት ቀን ተከታትሎ ገለዓድ በተባለ ኰረብታማ አገር ደረሰበት።

24. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሶርያዊው ለላባ በሕልም ተገልጦ፣ “ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ፣ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው።

25. ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኰረብታማ አገር ድንኳኑን ተክሎ ሳለ፣ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም በዚያው ሰፈሩ።

26. ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ምን ማድረግህ ነው? አታልለኸኛል፤ ልጆቼን የጦር ምርኮኛ ይመስል አካልበህ ወሰድሃቸው።

27. ለመሆኑ ለምን ተደብቀህ ሄድህ? ለምንስ አታለልኸኝ? ብትነግረኝ ኖሮ፣ በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና አልሸኝህም ነበር?

28. የልጆቼን ልጆችና ልጆቼንም ስሜ ብሰናበት ምን ነበረበት? የሠራኸው የጅል ሥራ ነው።

29. ልጐዳችሁ እችል ነበር፤ ዳሩ ግን ባለፈው ሌሊት የአባታችሁ አምላክ (ኤሎሂም) ‘ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ አለኝ።

30. አንተ ወደ አባትህ ቤት ለመመለስ ስለ ናፈቅህ ሄደሃል፤ ነገር ግን የቤቴን የጣዖት ምስል የሰረቅኸው ለምንድ ነው?”

31. ያዕቆብም ለላባ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ሴቶች ልጆችህን በኀይል ነጥቀህ ታስቀርብኛለህ ብዬ ስለ ፈራሁ ነው።

32. ነገር ግን ከእኛ መካከል የአንተን የጣዖታት ምስል ደብቆ የተገኘ ሰው ካለ ይሙት። ያንተ የሆነ አንዳች ነገር ከኔ ዘንድ ቢገኝ፣ አንተው ራስህ ዘመዶቻችን ባሉበት ፈልግና ውሰድ።” ይህን ሲል፣ ራሔል የጣዖታቱን ምስል መስረቋን ያዕቆብ አያውቅም ነበር።

33. ላባም ወደ ያዕቆብ፣ ድንኳንና ወደ ልያ ድንኳን እንዲሁም ወደ ሁለቱ ደንገጡሮቿ ድንኳኖች ገባ፤ ነገር ግን ምንም አላገኘም። ከልያ ድንኳን ከወጣ በኋላ ወደ ራሔል ድንኳን ገባ።

34. ራሔል የጣዖታቱን ምስል ከግመሏ ኮርቻ ሥር ሸሽጋ፣ በላዩ ተቀምጣበት ነበር፤ ላባም ድንኳኑን አንድ በአንድ በርብሮ ምንም ሊያገኝ አልቻለም።

35. ራሔልም አባቷን፣ “በፊትህ ተነሥቼ መቆም ስላልቻልሁ፣ ጌታዬ አትቈጣ፤ የወር አበባዬ መጥቶ ነው።” አለችው፤ ስለዚህ በረበረ፤ የጣዖታቱን ምስል ግን ማግኘት አልቻለም።

36. በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ተቈጣ፤ ላባንም እንዲህ ሲል ወቀሰው፤ “እስቲ ወንጀሌ ምንድን ነው? ይህን ያህል የምታሳድደኝ ኀጢአቴ ምን ቢሆን ነው?

37. ዕቃዬን አንድ በአንድ በርብረሃል፤ ታዲያ፣ የአንተ ሆኖ ያገኘኸው ዕቃ የትኛው ነው? ካለ፣ እስቲ በአንተም በእኔም ዘመዶች ፊት አቅርብና እነርሱ ያፋርዱን።

38. ሃያ ዓመት አብሬህ ኖሬአለሁ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከመንጋህ አንድ ጠቦት እንኳ አልበላሁም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31