ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:18-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደ ፊት አስቀደመ፤ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጒዞውን ቀጠለ።

19. ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ሳለ፣ ራሔል የአባቷን ቤት የጣዖታት ምስል ሰረቀች።

20. ያዕቆብም ቢሆን፣ መኰብለሉን ለሶርያዊው ለላባ ሳይገልጥለት በመቅረቱ አታልሎታል።

21. ያዕቆብ የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይዞ፣ የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኰረብታማው አገር፣ ወደ ገለዓድ አመራ።

22. የያዕቆብ መኰብለል ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው።

23. ላባ ዘመዶቹን ይዞ ተነሣ፤ ያዕቆብንም ሰባት ቀን ተከታትሎ ገለዓድ በተባለ ኰረብታማ አገር ደረሰበት።

24. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሶርያዊው ለላባ በሕልም ተገልጦ፣ “ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ፣ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው።

25. ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኰረብታማ አገር ድንኳኑን ተክሎ ሳለ፣ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም በዚያው ሰፈሩ።

26. ከዚያም ላባ ያዕቆብን እንዲህ አለው፤ “ምን ማድረግህ ነው? አታልለኸኛል፤ ልጆቼን የጦር ምርኮኛ ይመስል አካልበህ ወሰድሃቸው።

27. ለመሆኑ ለምን ተደብቀህ ሄድህ? ለምንስ አታለልኸኝ? ብትነግረኝ ኖሮ፣ በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና አልሸኝህም ነበር?

28. የልጆቼን ልጆችና ልጆቼንም ስሜ ብሰናበት ምን ነበረበት? የሠራኸው የጅል ሥራ ነው።

29. ልጐዳችሁ እችል ነበር፤ ዳሩ ግን ባለፈው ሌሊት የአባታችሁ አምላክ (ኤሎሂም) ‘ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ’ አለኝ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31