ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:16-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ከአባታችን ወስዶ ለአንተ የሰጠው ሀብት ሁሉ የእኛና የልጆቻችን ነው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የነገረህን ሁሉ አድርግ።”

17. ከዚያም ያዕቆብ ልጆቹንና ሚስቶቹን ግመሎች ላይ አስቀመጠ፤

18. በመስጴጦምያ ካፈራው ሀብት ሁሉ ጋር ከብቶቹን በሙሉ ወደ ፊት አስቀደመ፤ ወደ አባቱም ወደ ይስሐቅ አገር፣ ወደ ከነዓን ምድር ጒዞውን ቀጠለ።

19. ላባ በጎቹን ሊሸልት ሄዶ ሳለ፣ ራሔል የአባቷን ቤት የጣዖታት ምስል ሰረቀች።

20. ያዕቆብም ቢሆን፣ መኰብለሉን ለሶርያዊው ለላባ ሳይገልጥለት በመቅረቱ አታልሎታል።

21. ያዕቆብ የእርሱ የሆነውን ሁሉ ይዞ፣ የኤፍራጥስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ኰረብታማው አገር፣ ወደ ገለዓድ አመራ።

22. የያዕቆብ መኰብለል ለላባ በሦስተኛው ቀን ተነገረው።

23. ላባ ዘመዶቹን ይዞ ተነሣ፤ ያዕቆብንም ሰባት ቀን ተከታትሎ ገለዓድ በተባለ ኰረብታማ አገር ደረሰበት።

24. ከዚያም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለሶርያዊው ለላባ በሕልም ተገልጦ፣ “ያዕቆብን፣ ክፉም ሆነ ደግ፣ እንዳትናገረው ተጠንቀቅ” አለው።

25. ያዕቆብ ገለዓድ በተባለው ኰረብታማ አገር ድንኳኑን ተክሎ ሳለ፣ ላባ ደረሰበት፤ ላባና ዘመዶቹም በዚያው ሰፈሩ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31