ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 31:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የላባ ወንዶች ልጆች፣ “ያዕቆብ የአባታችንን ሀብት እንዳለ ወስዶታል፤ ይህ ሁሉ እርሱ ያካበተውም ሀብት ከአባታችን የተገኘ ነው” እያሉ ሲያወሩ ያዕቆብ ሰማ።

2. የላባ አመለካከት ከቀድሞው የተለወጠበት መሆኑንም ያዕቆብ ተረዳ።

3. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ያዕቆብን፣ “ወደ አባቶችህና ዘመዶችህ አገር ተመለስ፤ እኔም ካንተ ጋር እሆናለሁ” አለው።

4. ስለዚህም ያዕቆብ መንጎቹ ወደ ተሰማሩበት መስክ እንዲመጡ፣ ራሔልንና ልያን አስጠራቸው፤

5. እንዲህም አላቸው፤ አባታችሁ ስለ እኔ ያለው አመለካከት እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ተረድቻለሁ፤ ቢሆንም የአባቴ አምላክ (ኤሎሂም) አልተለየኝም፤

6. መቼም ባለኝ ዐቅም አባታችሁን ማገልገሌ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም።

7. አባታችሁ ደሞዜን ዐሥር ጊዜ እየለዋወጠ አታልሎኛል፣ ሆኖም እንዲጎዳኝ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አልፈቀደለትም።

8. እርሱ፣ ‘ደሞዝህ ዝንጒርጒሮቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ዝንጒርጒር ወለዱ፤ ደግሞም ‘ደሞዝህ ሽመልመሌዎቹ ይሆናሉ’ ሲለኝ፣ መንጎቹ ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸውን ወለዱ፤

9. ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የአባታችሁን ከብቶች ወስዶ ለእኔ ሰጠኝ።

10. “እንስሳቱ በሚጠቁበት ወራት፣ የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች መልካቸው፣ ሽመልመሌ፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ዐይኔን አንሥቼ በሕልሜ አየሁ።

11. የእግዚአብሔርም (ኤሎሂም) መልአክ፣ ‘ያዕቆብ’ አለኝ፤ እኔም፣ ‘እነሆ አለሁኝ’ አልሁት።

12. እርሱም ‘መንጎቹን የሚያጠቋቸው አውራ ፍየሎች ሁሉ ሽመልመሌ መልክ ያላቸው፣ ዝንጒርጒርና ነቍጣ ያለባቸው መሆናቸውን ቀና ብለህ ተመልከት፤ ላባ በአንተ ላይ የሚፈጽመውን ድርጊት ሁሉ አይቻለሁና፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 31