ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 30:14-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. ስንዴ በሚታጨድበት ወቅት፣ ሮቤል ወደ ሜዳ ወጣ እንኮይም አግኝቶ ለእናቱ ለልያ አመጣላት። ራሔልም ልያን፣ “እባክሽን ልጅሽ ካመጣልሽ እንኮይ ስጪኝ” አለቻት።

15. ልያም፣ “ባሌን የቀማሽኝ አነሰና የልጄን እንኮይ ደግሞ ልትወስጂ አማረሽ?” አለቻት።ራሔልም፣ “ስለ ልጅሽ እንኮይ ዛሬ ከአንቺ ጋር ይደር” አለቻት።

16. በዚያች ምሽት ያዕቆብ ከዕርሻ ሲመለስ፣ ልያ ወጥታ ተቀበለችውና፣ “በልጄ እንኮይ ስለ ተከራየሁህ የዛሬው አዳርህ ከእኔ ጋር ነው” አለችው፤ ያዕቆብም በዚያች ሌሊት ከእርሷ ጋር አደረ።

17. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የልያን ጸሎት ሰማ፤ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም አምስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች።

18. ልያም፣ “አገልጋዬን ለባሌ በመስጠቴ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ክሶኛል” አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ አወጣችለት።

19. ልያ አሁንም ደግማ ፀነሰች፤ ለያዕቆብም ስድስተኛውን ወንድ ልጅ ወለደች።

20. እርሷም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በከበረ ስጦታ ዐድሎኛል፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት፣ ከእንግዲህ ባሌ አክብሮ ይይዘኛል”። አለች፤ ስሙንም ዛብሎን አለችው።

21. ከዚያም በኋላ ሴት ልጅ ወለደች፤ ስምዋንም ዲና አለቻት።

22. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ራሔልን ዐሰባት፤ ልመናዋንም ሰምቶ ማሕፀንዋን ከፈተላት።

23. ከዚያም ፀንሳ፣ ወንድ ልጅ ወለደችና “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዕፍረቴን አስወገደልኝ” አለች፤

24. ስሙንም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ ስትል፣ ዮሴፍ” አለችው።

25. ራሔል ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፤ “ወደ ገዛ ቤቴ፣ ወደ አገሬ እንድመለስ አሰናብተኝ፤

26. የድካሜ ዋጋ የሆኑትን ሚስቶቼንና ልጆቼን ስጠኝና ይዤአቸው ልሂድ፤ መቼም የቱን ያህል እንዳ ገለገልኹህ ታውቃለህ” አለው።

27. ላባም እንዲህ አለው፤ “በጎ ፈቃድህ ቢሆን፣ እባክህ እዚሁ ከእኔ ጋር ተቀመጥ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔርም (ያህዌ) በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ በንግርት ተረድቻለሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 30