ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 28:7-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ያዕቆብ የአባት የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ።

8. በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤

9. ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ።

10. ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ።

11. ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ።

12. በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ።

13. እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ (ኤሎሂም)፣ የይስሐቅ አምላክ (ኤሎሂም) እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ።

14. ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ።

15. እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።”

16. ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር (ያህዌ) በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ።

17. እርሱም በፍርሀት፣ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህስ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቤት መሆን አለበት፤ የሰማይ ደጅ ነው” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 28