ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 27:3-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. ስለዚህ የአደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰሮጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ።

4. ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።”

5. ይስሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣

6. ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣

7. ‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤

8. ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ።

9. ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ፣ የሚወደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤

10. እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ፣ ይዘህለት ግባና ይብላ።”

11. ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጒራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው።

12. ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።”

13. እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።

14. እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት።

15. ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው።

16. እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው።

17. ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው።

18. ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ፤ አለ፤ ይስሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 27