ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 27:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ይስሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው።እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።

2. ይስሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን ዐላውቅም

3. ስለዚህ የአደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰሮጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ።

4. ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።”

5. ይስሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣

6. ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣

7. ‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤

8. ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ።

9. ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ፣ የሚወደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤

10. እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ፣ ይዘህለት ግባና ይብላ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 27