ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 25:23-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አላት፤“ወገኖች በማሕፀንሽ አሉ፤ሁለትም ሕዝቦች ከውስጥሽ ተለያይተው ይወጣሉ፤አንደኛው ከሌላው ይበረታል፤ታላቁም ለታናሹ አገልጋይ ይሆናል” አላት።

24. የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስም፣ እነሆ፤ በማሕፀንዋ መንታ ወንዶች ልጆች ነበሩ።

25. በመጀመሪያ የተወለደው መልኩ ቀይ፣ ሰውነቱም በሙሉ ጠጒር የለበሰ ነበር፤ ስለዚህ ስሙ ዔሳው ተባለ።

26. ከዚያም ወንድሙ ተወለደ፤ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ወጣ፤ ከዚህም የተነሣ ስሙ ያዕቆብ ተባለ። ርብቃ ልጆቿን ስትወልድ፣ ይስሐቅ የሥልሳ ዓመት ሰው ነበር።

27. ልጆቹም አደጉ፤ ዔሳው ጐበዝ ዐዳኝ፣ የበረሓም ሰው ሆነ፤ ያዕቆብ ግን ጭምት፣ ከድንኳኑ የማይወጣ ሰው ነበር።

28. ይስሐቅ ከዐደን የመጣ ሥጋ ደስ ይለው ስለ ነበር፣ ዔሳውን ይወደው ነበር፤ ርብቃ ግን ያዕቆብን ትወደው ነበር።

29. አንድ ቀን ያዕቆብ ወጥ እየሠራ ሳለ ዔሳው እጅግ ተርቦ ከዱር መጣ።

30. ዔሳውም ያዕቆብን፣ “ቶሎ በል፤ በጣም ርቦኛልና ከዚህ ቀይ ወጥ አብላኝ” አለው። ስለዚህም ስሙ ኤዶም ተባለ።

31. ያዕቆብም፣ “በመጀመሪያ ብኵርናህን ሽጥልኝ” አለው።

32. ዔሳውም፣ “እነሆ፣ ልሞት ደርሻለሁ፤ ታዲያ ብኵርናው ምን ያደርግልኛል!” አለ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 25