ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 24:52-65 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

52. የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰገደ።

53. ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው።

54. እርሱና አብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ፤በማግስቱ ጠዋት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ።

55. ወንድሟና እናቷም፣ “ልጂቷ ከእኛ ጋር ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ ትችላለች።” ብለው መለሱ።

56. እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው።

57. እነርሱም፣ “ለማናቸውም ልጂቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ።

58. ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋር መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት።እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች።

59. ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋር፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና አብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው።

60. ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤“እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”።

61. ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ።

62. በዚህን ጊዜ፣ ይስሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር።

63. እርሱም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ።

64. ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይስሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤

65. አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው።አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 24