ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 24:11-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጒድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ጥላ የበረደበት፣ ሴቶች ውሃ ለመቅዳት የሚወጡበት ነበር።

12. ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጒዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው፤

13. እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ።

14. እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘እንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይስሐቅ የመረጥካት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”

15. እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። እርሷም ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ነበረች።

16. ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያልደረሰባት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች።

17. አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።

18. እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው።

19. እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች።

20. ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጒድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው።

21. አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) መንገዱን አሳክቶለት እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጂቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር።

22. ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውዬው ግማሽ ሰቅል የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 24