ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 21:24-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. አብርሃምም፣ “እሺ፤ እምላለሁ” አለ።

25. ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮቹ ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጒድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት።

26. አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው።

27. ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ።

28. አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤

29. አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድ ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።

30. አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጒድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች እንካ ተቀበለኝ” አለው።

31. ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ ተባለ።

32. በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ።

33. አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም የዘላለም አምላክን (ኤል ኦላም) ስም ጠራ።

34. አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረጅም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 21