ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ዘፍጥረት 20:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን?

5. ‘እኅቴ ናት’ ያለኝ ራሱ አይደለምን? ደግሞስ ራሷም ብትሆን፣ ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረግሁት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።”

6. እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በሕልሙ እንዲህ አለው፤ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው።

7. አሁንም ሚስቱን ለሰውዬው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ።”

8. በማግስቱም ማለዳ፣ አቢሜሌክ ሹማምቱን ሁሉ ጠርቶ፣ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነርሱም ታላቅ ፍርሀት አደረባቸው።

9. ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣብህን? በእውነቱ መደረግ የማይገባውን ነው ያደረግህብን።”

10. ከዚያም አቢሜሌክ፣ “ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።

11. አብርሃምም አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “እዚህ ቦታ ፈሪሀ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አለመኖሩን ተገነዘብሁ፤ ሰዎቹም ለሚስቴ ሲሉ ይገድሉኛል ብዬ ሠጋሁ፤

12. ደግሞም እኮ በእርግጥ እኅቴ ናት፤ ከአንድ እናት ባንወለድም በአባት አንድ ነን፤ ኋላም አገባኋት።

13. እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አዞኝ ከአባቴ ቤት ወጥቼ በየአገሩ ስዞር፣ ‘ለእኔ ያለሽን ፍቅር በዚህ ግለጭልኝ፤ በየደረስንበት ስፍራ ሁሉ “እርሱ ወንድሜ ነው” በዪ’ ብያት ነበር።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ዘፍጥረት 20